የሸካ ዞን አጠቃላይ ገጽታ

zoneb: 

የዞኑ አስትሮኖሚያዊና አንጻራዊ መገኛ
የሸካ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ 5 ዞኖች አንዱ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በላቲትዩድ መስመር 7.12-7.89 ዲግሪ ሰሜን ሎንግቲዩድ መስመር 35.24-37.90 ዲግሪ ምስራቅ የሚገኝ ሲሆን አዋሳኞቹም በሰሜን ከኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ዞን በደቡብ ከቤንች ማጂ ዞን በምስራቅ ከካፉ ዞን በምዕራብ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ናቸው፡፡
የዞኑ ቆዳ ስፋት
የዞኑ ቆዳ ስፋት 238750 ሄ/ር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 61.7% በደን የተሸፈነ ሲሆን የዚህም ዋነኛ ምክንያት የህሰቡ ጠንካራ የደን ጥበቃ ባህል ለረዥም ጊዜ ጠብቆ ያቆየው ነው፡፡ ከሌሎች መሬት አጠቃቀም አንፃር በሰብል 67184.25 ሄ/ር እና በተለያዩ የመሬት አጠቃቀም የተያዘ 24782.25 ሄ/ር የተሸፈነ ነው፡፡
የአየር ሁኔታ
ዞኑ በ3 ወረዳ፣ በ2 ከተማ አስተዳደር፣ በ7 ታዳጊ ማዘጋጃ ቤቶች እና በ57 የገጠርና በ5 የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀረ ነው፡፡ የዞኑ አየር ንብረት 18% ደጋ፣ 60% ወይናደጋ፣ 22% ቆላ ሆኖ አማካይ የዝናብ መጠን በዓመት 1800-2200 ሚ.ሜ ሲሆን ዞኑ ከባህር ጠለል በላይ ከ900-2700 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡
የሚመረቱ ምርቶች
የዞኑ ህ/ሰብ በጥምር እርሻ የሚተዳደር ሲሆን ከሚያለማቸው ሰብሎች ዋና ዋናዎቹ እንሰት፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ዳጉሣ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ቡና፣ ቅመማቅመም፣ የተላያዩ አትክልት ዓይነቶች፣ ፍራፍሬዎች እና የተለያዩ የሥራሥር ዓይነቶች ናቸው፡፡
የህዝብ ቁጥርና አሰፋፈር
በ1999 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትና የህዝብ ዕድገት መካከለኛ ግምት መሰረት በ2007 ዓ.ም የዞኑ ህዝብ ብዛት 255704 ሲሆን ከዚህም ውስጥ ወ.129732 ሴ.125972 ሲሆን 60% በቀጥታ በእንሰት የምግብ ፍጆታውን የሚሸፍን ነው፡፡