የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦቸ ክልል ምክር ቤት አባላት በቀረበው የአስፈጻም አካላት ሪፖርት ላይ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦቸ ክልል ምክር ቤት አባላት በቀረበው የአስፈጻም አካላት ሪፖርት ላይ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦቸ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በክልሉ በበጀት አመቱ የተሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አመርቂ መሆናቸውን ተናግረው በተለይ ከነባሩ የደቡብ ክልል የተሻገሩ ያደሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በዚህም በመንገድ፣ በውሃ፣ በድልድይ እና በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ ክልሉ የጀመረው ስራ አበረታች ቢሆንም በካፋ ዞን ጎባ እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ ዞን የሱሪ-ቤሮ መንገድ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል።
በጤናው ዘርፍ ከበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ረገድ በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ስራዎች ላይ ውስንነት እንዳለ የተነሳ ሲሆን በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት አሳሳቢ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሰራ እንዳለም ተነስቷል።
በአስተዳደር ዘርፍ በተሰራው ተግባር በክልሉ አንጻራዊ ሠላም ማስፈን መቻሉን የገለጹት የምክር ቤት አባላት በምዕራብ ኦሞ ዞን ያለው የፀጥታ ችግር በዘላቂነት መንግሥት እንዲፈታው ጥያቄ አቅርበዋል።
የክልሉን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነትን ለማሳለጥ ፋይዳ ያላቸው መንገዶች የኮንታ- ጠሎ መንገድ ፤ ቤንች ሸኮን ከምዕራብ ኦሞ የሚያገናኘው መንገድ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል።
በትምህርት ዘርፍ በተላይ ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ አመርቂ ስራ እየተሰሩ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የዘመናት ጥያቄ የነበረው የናኦ እና ጫራ ብሄረሰብ በራስ ቋንቋ የመማር መብት በተግባር መረጋጡ የተነሳ ሲሆን በቀጣይ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ይህ ተግባር ተጠናክሮ ከማስቀጠል አንጻር ያለው ዝግጅት ተጠይቋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተላይ የእርሻ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ ክልሉ የጀመረው ተግባር የሚደነቅ መሆኑ ተመላክቶ በክልሉ ያለው ከፍተኛ የአሲዳማ አፈርን ከማከም አንጻር በቀጣይ ምን እንደታሰበ ከምክር ቤቱ ጥያቄ ቀርባል።
ከከተማ ልማት ስራዎች አንጻር በከተሞች እየተበራከተ የመጣውን ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ካሉ እንዲብራራም በመጠየቅ በዚህ ዘርፍ በከተሞች የፈርጀ ዕድገት ከሁለት ወደ ፈርጅ አንድ ለምን ከተሞችን ማሳደግ እንዳልተቻለ ጥያቄ ቀርቧል።
በመንገድ ዘርፍ በመንግሥት አቅም እንዲሁም ህብረተሰብን በማስተባበር የተሻሉ ተግባራት መመዝገቡን የተናገሩት የምክር ቤት አባላት በተላይ በህብረተሰብ ተሳትፎ በሚሰሩ መንገዶች ላይ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ከፐብለክና ሰው ሀብት ስራዎች አንጻር ያለውን ውስን የመንግሥት ሀብተ ለማስተዳደር መንግሥት የጀመረው አዲሱ የሠራተኛ ድልድል ተገቢ መሆኑን የተናገሩት የምክር ቤቱ አባል በዚህም በአፈጻጸም ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮች በትኩረት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች በተሰሩ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን የምክር ቤቱ አባላት በማንሳት በየአካባቢው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍሃዊነት እና ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት አልቆ የአስፈጻሚ አካላት ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።